Sunday, 12 August 2012

በድር ኢትዮጵያ


በድር ኢትዮጵያ
ሰላማዊ ትግልን በእስርና በእንግልት ማጨናገፍ ከቶውንም አይቻልም::

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ትግል ከጀመሩ ስምንተኛ ወራቸውን አስቆጥረዋል:: ይህ በአፍሪካ ወደር ያልተገኘለት ህገ መንግሥታዊን መብት የማስከበር ሂደት ለሰላማዊ ሂደቱ አድናቆትን ችሮ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ፈንታ መንግስት እየተከተለ ያለው አቅጣጫ ከታሪክ ተጠያቂነት አያድነውም::

እንኳን ለዲሞክራሲ ታግያለው ከሚል ቀርቶ አምባገነኖች የማይተገብሩት ተግባር በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ይገኛል::
ትላንት በአወሊያ ለሰደቃ ፕሮግራም በተዘጋጁ ሰዎች ላይ ከዚያም በአንዋር መስጊድ ሰላማዊ ተቃውሞ ባደረጉት ላይ የደረሰው እንግልት፡ድብደባ እና እስር ቁስሉ ሳይደርቅ ዛሬ በደሴ አረብ ገንዳ ለአርብ ሰላት በተሠበሠቡ ምዕመናን ላይ የደረሰው እንግልት እና እስራት እጅጉን አሳዝኖናል:: በሀገሪቷ ውስጥ ያሉ መሪዎች እንዴት ቆም ብለው ለህዝቡም ለሃገሪቷም የሚበጅ ነገር ማምጣት አለማቻላቸው የደገሱት ነገር አስከፊ መሆኑን አመላካች ነው::

ህዝቦችን በማታለል በመግፋት ያላሉትን በማለት በቴሌቪዥን በማሣየት ህብረተሠብን ማደናገር እና የህብረተሠቡ አቋም እንደሆነ መስበክ ራስን መሸንገል(Self-denial)እንጂ ከቶውንም ሌላ ምህጻረ ቃል አይገኝለትም:: ትላንት በህዝብ የተወከሉ ኮሚቴዎችን፤ዳኢዎችን እና ጋዜጠኞችን በማሠር ትግሉን አስቆምን ባሉ ማግስት ሙስሊሙ ህብረተሠብ ድምጻችን ይሰማ በማለት ከዳር እስከ ዳር ሰላማዊ ትግሉን አቀጣጥሎዋል::

የመሪዎቹ መታሠር ያነሳውን የመብት ጥያቄ አላስቆመውም ይዋል ይደር እንጂ አላህ ለባሮቹ ቃል የገባውን ድል ይሰጣቸዋል::

በድር ኢትዮጵያ በደሴ በአላባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላማዊ የሃይማኖታዊ ጥያቄ በጠየቁ ወገኖች ላይ የመንግስት ኢሰብአዊ ማንገላታት እና እሥራት በጽኑ እያወገዝን ሰላማዊ ትግልን በእስርና በእንግልት ማጨናገፍ እንደማይቻል መልዕክታችንን እናስተላልፋለን::

በድር ኢትዮጵያ አሁንም ሰላማዊውን ትግል ከልብ እንደሚደግፍ በድጋሚ ያረጋግጣል::

አላሁ አክበር!!
በድር ኢትዮጵያ
ዋሽንግተን ዲሲ

No comments:

Post a Comment