Tuesday, 14 August 2012

Meranu Habibti United Voice of Ethiopian Muslims Against Ahbash

Meranu Habibti United Voice of Ethiopian Muslims Against Ahbash
አንዋር መስጅድ በተክቢር ሲደምቅ አረብ ገንዳ በጭፍጨፋ ተናጠች
ቢስሚላሂረህማኒረሂም፡፡ትላንት የአንዋር መስጅድን ዉሎ በተመለከተ አጭር ቅኝት ለመጻፍ ፍላጎቱ ቢኖረኝም ዉስጤ ግን ፍፁም ሰላም አልነበረውምና ያንን ማድረግ አልተቻለኝም፡፡መቸም አእምሮ ሰላም ካልሆነ ሌላውም የሰውነት ክፍሎች ምቾት አይሰማቸውምና ጣቶቼ ከኪቦርዱ ላይ አርፈው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ አልተቻላቸውምና የአንዋር መስጅድን ዉሎ በተመለከ ትላንት ልፅፈው የነበረው አጭር ማስታወሻ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ዛሬም ቢሆን ስሜቱ አለቀቀኝም፡፡ግና አንዳንድ ነገረ ለማለት የግድ ስለሆነብኝ እንጂ፡፡መቼም ይህ ሁሉ ቁዘማ ለምን እንደሆነ ሳትረዱኝ አልቀራችሁም፡፡እኔ ውስጥ ያለው ስሜትም እናንተ ውስጥም የለም ለማለትም አይቻለኝም፡፡ይህ ሁሉ የስሜት መድማት የተከሰተው ደግሞ ትላንት በደሴ አረብ ገንዳ መስጅድ በንፁሃንና ሰላማዊ ዜጎች ላይ በመንግስተ ሃይሎች የተየተፈፀመው አሳፋሪና ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል ነው፡፡ይህ ሰይጣናዊ ድርጊት ደግሞ ሙስሊሞችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እውነተኛ ኢተዮፒያዊያንን ሁሉ ያሳዘነ ነበር፡፡

በአንዋር መስጅድ የጁሙዐ ሰላት ለማድረስ በመሰጅዱ ስላለሁ እንደወትሮዬ እንደማደርገው ስልኬን ሳይለንት አድረጌዋለሁ፡፡ትኩረቴ ሁሉ በመስጅዱ ዙሪያ ባለው ትእይንት ላይ ነው፡፡አንዋር መስጅድ ከስከዛሬው እጅግ በርካታ ህዝብ እንደተገኘ ከመስጂዱ የተለያ አቅጣጫ የተቀረፁ የፎቶና ቪዴዮ ማስረጃዎችን ማየቱ በቂ ነው፡፡ያለማጋነን በሚሊዮን የሚቆጠር ሀዝብ ተገኝቷል፡፡ከፒያሳ ሲነሱ ኩርቱ ህንፃጋ መቆም የግድ ይልዎታል፡፡ምክንያት ቢሉ ሰጋጁ እዛ ደርሷልና፡፡ከአውቶቡስተራ ሲነሱ ሜይዴይ ትምህርት ቤት ላይ ይቆማሉ፣በመርካቶ ጣና ገበያን አልፎ ምዕራብ ሆቴል ተዳርሷልፈ፣ወደታች ደሞ ሲዳሞ ተራን አልፏል፣ከወደ ጥቁር አንበሳ ሲመጡ ተክለሃይማኖት አደባባይ ሲደርሱ የሰዉ ብዛት ያቆምዎታል፡፡አልሃምዱሊላህ፡፡ይህ ሁሉ እንግዲህ በአዲስ አበባ ያሉ ከመቶ ሃያ በላይ መስጅዶችን ሰጋጆች ሳይጨምር ነው፡፡ታዲያ ይህ ሁሉ ሰው ላይ የሚያነቡት ስሜት አንድ አይነት ነው፡፡ዞር ብለው ከጎንዎ ያለውን ሰጋጅ ዐይን ቢመለከቱ የእርስዎ አይን ዉስጥ የሚታየውን አይነት ነገር ነው የሚያዩት፡፡ሁለታችሁም አይን ውስጥ ድምፃን ይሰማ የሚል ስሜት ያለው ቋንቋ ይነበባል፡፡ነገሩ ምንም ሳይጋነን ሚሊዮኖች አንድ ነበሩ የሚለው አነጋገር ይገልፃቸዋል፡፡ለዚህ አገላለፅ ደሞ ማስረጃ አለ፡፡ግዴለም ጥቂት ይጠብቁ፡፡አሁን የመስጅዱ ኢማም ሁጥባ ላይ ስለሆኑ ነው፡፡ተሰግዶ ሲያበቃ ታያላችሁ፡፡በዚህ ሁላ መሃል ግን ተሰግዶ እስኪጨርስ ሳይለንት ያደረኩት ስልኬ ከወደ ደሴ የጩሀት ጥሪ ይጣራል፡፡እኔ ከየት ሰምቸው?ይልቅ ሃሳቤን ሌላ ነገር ሰረቀው፡፡ከጎኔ ያሉት ሁለት ወጣቶች በሆነ ነገር ተገርመው ይንሾካሾካሉ፡፡ጃቸውንም በሆነ ሰው ላይ ይጠቁማሉ፡፡ነገሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ ለመጠየቅ ወብፈልግም ሁጥባ እየተሆጠበ ነውና ዝምታን መረጥሁ፡፡አሁን ሁጥባው ተጠናቆ ለሰላት እንድንቆም ታዘዝን፡፡በዚህች ቅፅበት ቅድም ድምፃቸውን ቀንሰው በአግራሞት ሲንሾካሾኩ የነበሩት ወጣቶች አሁን በግልፅ ጮክ ብለው ወደአንድ ሰው አየጠቆሙ ሰውየው ሙስሊም እንዳልሆነ፣ይልቅ አንደኛው ወጣት በሚኖርበት ክፍለ ከተማ አመራር አንደሆነ ተናገረ፡፡አሃ ተሰልሎ ተሙቷል፡፡አንዳንዶች ከዚህ እናስወጣው ሲሉ አብዛኛው ደሞ “ተዉት መን አንደሚያደርግ እንየው” በሚል መጨረሻውን ለማየት ፈለጉ፡፡አሁን ካድሬውን(ሰላዩን አንበለው?) ለግዜው እርሱት፡፡ምክናቱም ስግደቱ ተጀምሯልና፡፡ስግደቱ ባለቀ በሃያ ሰከንዶች ውስጥ ቅድም ያልኳችሁ አንድነት ታየ፡፡ሁሉም ካለበት ሳይነሳ ነጭ ወረቀቶችን ማውለብለብ ተጀመረ፡፡ኢስላም ሰላም ነው አለ፡፡እውነትም ሰላም ነው፡፡በሰለጠነ መንገድ ጥያቄውን ቢጠይቅም የሰለጠነ መንግስት የለውምና ይሃውና አሁንም ጥያቄ ላይ ነው፡፡ነጭ ወረቀቱ ተውለብልቦ እንዳበቃ ድንገት ተክቢር ተጀመረ፡፡ሱብሃነላህ፡፡የተክቢራው አመጣጥ እራሱ Artistic (ጥበብ የተለባሰ)ነው፡፡ተክቢራው እጅግ ከራቀ አካባቢ እንደማዕበል የሚመጣ ነው የሚመስለው፡፡ድፍን አዲስ አበባ ነው እንዴ ተክቢራ እያለ ያለው?ስል አሰብኩ፡፡የሆኖ ሆኖ ተክቢራው በድምቀት ቀጠለ፡፡ሳይለንት ያደረኩት ስልኬም ከወደ ደሴ እሪታውን ያቀልጠዋል፡፡እኔ ግና ከየት ብዬ ሰምቼው?ተክቢሩ አሁንም ቀልጧል፡፡በዛች ቅፅበት ደሞ በደሴ አረብ ገንዳ መስጅድ ሰላማዊ ወገኖቼ በህገ ወጦቹ እየተቀጠቀጡ አንደነበር ማናችንም አላወቅንም ነበር፡፡ከተክቢሩ በኋላ ድምፃችን ይሰማ ፣ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ ፣ምርጫችን በመስጅዳችን የሚሉ የተቃውሞ መፈክሮች ለበርካታ ደቂቆች ተሰሙ፡፡በመጨረሻ ዱዐ ተደርጎ ሰዉ በሰላማዊ መንገድ ተበተነ፡፡ሰጋጅ ካድሬውም አብሮን ተበተነ፡፡የሚያውቁት ለምን እንደመጣ ሊያናግሩት ፍላጎት ቢያድርባቸውም በሌሎች ሰዎች ተከለከሉ፡፡”ተዉት ሄዶ ያየውን ይንገራቸው፣ሙስሊሙ ግን ጠላቶቹን እየለየ በሞሆኑ አጋጣሚው መልካም ነው ”ሲሉ አንዳንዶች ለመምከር ሞከሩ፡፡በኋላ ባገኘሁት መረጃ በሴቶች መስጀድ ውሰጥም በርካታ የወረዳና ክፍለከተማ ሙስሊም ያልሆኑ ሴት ካድሬዎች እንደታዩ ምንጮች ጠቁመውኛል፡፡ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ ሙስሊሞችም ሆኑ ሙስሊም ያልሆናችሁ ኢትዮፕያውያን ከጎናችሁ ሆነው በማትረባ ጥቅም(ሊያውም ዘላቂ ያልሆነ)ጥቅም ብለው ወገኖቻቸውን ለማስጨረስ ላይ ታች የሚሉ በውስጣችን ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክፍለከተማ ያሉ ደም የጠማቸው ካድሬዎችን እጅግ እንድንጠነቀቃቸው ያስፈልጋል፡፡መቼም አይናችን እያየ እጃችንን አስኪሰጡን መጠበቅ የለብንም፡፡ከታሪክ ሊማሩ ይገባል፡፡የምናውቃቸው ካድሬዎች ካሉ እናስመክራቸው፡፡ካድሬዎች ምክር የገባችሁ እንደሆነ ተመከሩ፡፡
ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ አስደናቂውና አዲስ አበባን ያደመቀ ሰላማዊ ተቃውሞው በሰላም በመጠናቀቁ ሁሉም አልሃምዱላህ ብሎ መበተን ጀመረ፡፡ሁኔታውን በተመለከተ ሙስሊም ያልሆነ አንድ የማውቀው ሰው እንደነገረኝ “የውነት ሙስሊሙ መንግሰትን ቀድሞት ሄዷል፡፡ይህ ሁላ ህዝብ ተሰብስቦ በአንድ አይነት ሰሜት አንድ አይነት ጥያቄ ጠይቆ ምንም ከመስመር ሳይወጣ በሰላም በመጠናቀቁ መንግሰትም ህዝብም ሊያከብራችሁ ይገባል”በማለት ነበር አድናቆቱን ሊገልፅልኝ የሞከረው፡፡ሆ አንተ ደሞ መንግስት ምሰጋናውን ትቶ ጥያቄያችንን በመለሰልን ስል ቀሬታዬን ገለፅኩለት፡፡ተሳሳትኩ እንዴ?
በዚህ መልኩ የተጠናቀቀው ሰላማዊ የተቃውሞ ሂደት እንዳለቀ ሰዉ ወደመጣበት ለመመለስ ደሞ ሌላ ሰላማዊ ሰልፍ አስመስሎት ነበር፡፡በዚህ መሃል ነበር አንግዲህ እኔም ስልኬን አውጥቼ ያየሁት፡፡ያለወትሮው ስልኬ በርካታ ሚስኮሎችን አጠራቅሟል፡፡ጥሪውን ስላላነሳሁላቸውም ሊሆን ይችላል 3 ቴክሰት ሜሴጆችንም አየሁ፡፡ከሚስኮሎቹ ይልቅ ሜሴጁን ስከፍተው “እየጨፈጨፉን ነው” የሚል ንባብ አገኘሁ፡፡ድንገት ቆምኩኝ፡፡የላከውን ሰው ቁጥር ስመለከት ደሴ ያለ ጓደኛ ነው፡፡ደወልኩለት አያነሳም፡፡ትግስት አጣሁ፡፡ሌሎች ከደሴ የደወሉ ሰዎች ጋር ሞከርኩ፡፡እነሱም እንደዛው፡፡ደሴ የሆነ መጥፎ ነገር እንደተከሰተ ብረዳም ማን ይንገረኝ?በኋላ እንደኔው ደሴ ሰው የሚያውኩ ሰዎች ከደሴ ተደውሎላቸው ታጣቂዎች አረብ ገንዳ መስጂድን አንደከበቡትና ሰዉን እየደበደቡት እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ድርጊቱ በጣም በጣም አሳፋሪ ድርጊት እንደሆነ የ 3 አመት ህፃን እንኳ ይረዳዋል፡፡እዚህ አዲስ አበባ የነበረው የሰዉ ስሜት ለመግለፅ ሁላ ይከብደኛል፡፡ክፉኛ ነበር ፊቱ እልህ የሚነበብበት፡፡ሃዘን ያጠላ ፊት የሚታይበት፡፡አብዛኛው ሰው ዱዐ ሁሉ ያደርግ ነበር፡፡አዎ ወላሂ በዱዐም አንለቃቸውም፡፡በደሴ እየሆነ ያለውን ሁኔታ በቂ መረጃ ለማግኘት ከደወሉልኝ ሰዎች መሃል አንዳቸውም ስልካቸውን ሊያነሱልኝ አልቻሉም ነበርና እጅግ ተጨነኩኝ፡፡ሳወጣ ሳወርድ ቆይቼ አንድ የማቃት እህት ጋር ደወልኩኝ፡፡አነሳችው፡፡ስለሁኔታው ስጠይቃት የለቅሶ ቅላፄ ባለው ቃና “ከተማውን በታጣቂዎች ወረውታል፡፡መትረየስ ባጠመዱ መኪኖች ጭምር ቀረራው የተካሄደው፡፡ጉድ ነው መስገጃ ብቻ ይዞ ከቤቱ ለወጣ ሰላማዊ ህዝብ በመስጅድህ መስገድ አትችሉም ተብሎ መትረየስ ሲደገንበት አስቡት እስኪ?የጤና ነው ትላላችሁ? በኋላ ከቦታው ካሉ ሰዎች በተገኘ መረጃ መሰረት ሆን ብሎ ድርጊቱን አስቦበት እንደፈፀመው ነው፡፡በአንድ ተራ ፖሊስ እዚህ ማንጠፍ አትችሉም በሚል ሰበብ በርካቶችን እህቶችና ወነድሞች ተቀጥቀጠው እንዲጎዱ ሆነዋል ፣የመስጂዱ ኢማምን ጨምሮ በርካቶችም ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል፡፡እዛ ምን እያደረጓቸው እንደሆነ ማን ያውቃል?አላህ ይደረስላቸው፡፡ይህ ደርጊት ታዝባቸሁት እንደሆነ ሆን ተብሎ እየመጡበት ያለ ስልት ነው፡፡የሙስሊሙ ሰላማዊነት እንደሚፈልጉት አላስኬዳቸውም እንጂ፡፡መጀመሪያ ላይ አሰሳ ላይ ጀመሩ፣ቀጥለው አዲስ አበባ አንዋርና አወሊያ፣አሁን ደሞ ደሴ አረብ ገንዳ፡፡ይህ አይነቱ ስልት በፖሌቲካ ቋንቋ የተወጣጠረን ነገረ ማስተንፈስ አንደሚባል የፖለቲካል ሳይንስ ተመራቂ ይናገራሉ፡፡ነገሩ ግር ሲለኝ የተመለከቱት እኝህ ምሁር “ፖሌቲከኞች አንድ የተወጣጠረ ነገር ሲገጥማቸው ከጥቅማቸው አኳያ ያዩትና የተወጣጠረው ያሉትን ነገር ሙሉ ለሙሉ ለማስተንፈስ ጉዳቱ የሚያመዝን ሆኖ ከተገኘ ወይም ሁኔታውን ሙሉ ለሙሉ ለማስተንፈስ አጋጣሚው ሳይመቻቸው የቀረ እንደሆነ ቀስ እያሉ በሂደት በትንሽ በትንሹ ሽብር በመፍጠርና የሰዉን ስሜት በመግደል ነገሩን የማስተንፈስና የማርገብ አካሄድ እንዳለ አጫወቱኝ፡፡ጉድ ነው፡፡እኛ እነሱ ማስተንፈስ ምናምን የሚሉት ነገር እኛ ከምንጠይቀው ፍትሃዊ ጥያቄ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ማን በነገረቸው?እኛ ሙስሊሞች ጥያቄያችን አስኪመለስ የሚረግብም፣የሚተነፍስም ነገር እንደሌለን ይወቁት፡፡ጥያቄያችን ዲናችንን በተመለከተ ፍትሃዊ ጥያቄ ነው፡፡ከዚህ ውጭ የምናውቅላቸው ነገር የለም፡፡ሙስሊሙ እነሱ በሚፈልጉት አቅጣጫ ሰላልሄደ አብደዋል፡፡ማበድ መብታቸው ነው፡፡እኛ አሁንም እንጮሃለን፡፡ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ፣ድጻችን ይሰማ፣ምረጫችን በመስጂዳችን፣አህባሽ በግድ አይጫንብን፡፡አላህ የታሰሩትን ወገኖች ይጠብቃቸው፣የተጎዱትን ያሽራቸው፣ሙስሊሙን ከጥቃት ይጠብቀን፣ሰላማዊና ፍትሃዊ ጥያቄ ስለጠየቅን ሴራ የሚጎነጉኑልንን ሴረኞችና ሙናፊቆችን አላህ መጨረሻቸውን ያፋጥንልን፡፡አሚን፡፡

No comments:

Post a Comment